የአበቅየለሽ ጠጅ፤ በቡርቧክሶች ዜማ

Abyssinia Business Network /ABN/

ጎንደር ከተማ ከመድረሳችን በፊት በማክሰኚትና በጠዳ መካከል እናገኛታለን፡፡ በመሰንቆ ጨዋታ የገነነችዋን መንደር፤ ቡርቧክስ እግር ጥሏችሁ ከመንደሯ ቤቶች ወደ አንደኛው ድንገት ጐራ ብትሉ ከሁለት እስከ አምስት የሚደርሱ መሰንቆዎችን የቤቱ ምሰሶ ላይ በክብር ተሰቅለው ታገኛላችሁ፡፡
የእማሆይ አበቅየለሽ ጥንታዊ ጠጅ ቤት የሚገኘው ጎንደር፤ ከፋሲል ግንብ ዋና መግቢያ በር ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ፣ ከዣን ተከል ዋርካ ወረድ ብሎ ነው፡፡ መኳንንቱና መሣፍንቱ – በአንገተ ረዥሙ የመጀን ብርሌ ‹አስናቀ› የሚባል ጠጅ (ዘመናዊውን ውስኪ ያስንቃል ለማለት ነው) ያንደቀደቁበት፤ የቡርቧክስ የመሰንቆ ጨዋታ የኮመኮሙበት ታሪካዊ ጠጅ ቤት ነው – እማሆይ አበቅየለሽ ጠጅ ቤት፡፡

አበቅየለሽ ይመር፤ በ1912 ዓ.ም. በጭልጋ ወረዳ ልዩ ስሙ ባርደምባ በሚባል ቀበሌ ከደብረ ምህረት እያሆ ቅድስት ማርያም ገዳም ተወለዱ፡፡ በ1934 ዓ.ም. ጎንደር ከተማ ገቡ፡፡ የጀመሩት የጥሩ ማር ጠጅ ጣይነት የንግድ ሥራ ከፍተኛ እውቅና አስገኝቶላቸዋል፡፡ ከጎንደር ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ አልፈው በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ስማቸውና ዝናቸው ናኘ፡፡ በኢትዮጵያ የኪነት ባለሙያዎችም ዘንድ ‹‹ጎንደር አበቅየለሽ›› እየተባለ ሲገጠምላቸውና ሲነገርላቸው ኖረዋል፡፡
አይቆረጠምም ደረቁ ባቄላ፣ አበቅየለሽ ጐንደር ፋርጣ የኔ ገላ፤


እመቴ አበቅየለሽ፣
(ከጠጁ፣ ከጮማው)
አታመጪው የለሽ!


አንድ ዕለት በለስ ቀንቶት እማሆይ አበቅየለሽ ጠጅ ቤት ተገኘሁ፡፡ እሳቸው የሉም፡፡ በ78 ዓመታቸው ነው ይህቺን ዓለም የተሰናበቷት፡፡ ትዝታቸውን ግን ጥለው አልፈዋል፡፡ ወደ ጠጅ ቤቱ ስትዘልቁ እርሳቸው በህይወት ሳሉ የሚቀመጡባት ቀይ ሶፋ፣ ከወንበሩ አጠገብ መቋሚያቸው፣ ከመቋሚያው አናት ላይ የእማሆይ አበቅየለሽ ይመር ባለ ጥቁርና ነጭ ፎቶግራፍ በክብር ተሰቅሎ ይጠብቃችኋል፡፡

https://issuu.com/abyssiniabusinessnetwork/docs/abyssinia_business_network_abn__feb_269694d9a64e46/44

በእድሜ የገፉ አዛውንቶች ወደ ጠጅ ቤቱ ሲዘልቁ ለአፍታ ቆመው፣ ባርኔጣቸውን አውልቀው ለቀይ ወንበሯ እጅ ይነሳሉ፡፡ ወንበሯ ላይ ማንም ሰው አይቀመጥም፡፡ አግራሞት ያጫረብኝ ደግሞ ጠጅ ጠግበው የሚወጡ እንግዶች ሁሉ የእማሆይ አበቅየለሽ ይመርን ‹መንበር› በክብር ተሰናብተው መውጣትን ፈጽሞ አለመዘንጋታቸው ነበር፡፡
እኛም የታሪኩ ተቋዳሽ ሆነን ጠጁን በመጀን ብርሌ አንደቀደቅነው፡፡ የእማሆይ አበቅየለሽ ጠጅ ቤት በመሰንቆ ጨዋታ ደምቋል፡፡ አዝማሪዎቹ፤ ቡርቧክሶች (ቤቱንም፤ ጠጪውንም) በፍቅር ‹‹እያሰከሩ›› ነው፡፡


ቀን አልታይ ብለሽ በሌት እደክማለሁ፣
የማገኝሽ መስሎኝ አፈር አሸታለሁ፡፡ …


ሆዴ ጭሶ ጭሶ የነደደ እንደሆን፣
ያመዱ መፍሰሻ ሥፍራው ወዴት ይሆን?!


ብጨርሰው ኖሮ ቅኔውን ተምሬ፣
ከዘረፉት እኩል እሆን ነበር ዛሬ፡፡


ዳኛውም ዝንጀሮ መፋረጃው ገደል፣
ከየት ላይ ተቁሞ ይነገራል በደል፡፡

እያጨበጨብን ገና ሳይናገር፣
ጠገብን እያልን ገና ሳይጋገር፣
አጨብጭቡ ሲሉን እያጨበጨብን፣
ነጋላቸው አሉን እኛ ጨልሞብን፡፡


ቢገፉን ቢገፉን ደረስነ ከገደል፣
ከ’ንግዲህስ ወዲያ ዙረን እንጋደል?!


ወንድሙን እየገፋ አድርሶ ከገደል፣
ለእምነቴ ቀናሁ ከበደልም በደል፣
ፈጣሪን መካድ ነው እንደገና መስቀል፤


ባይወጉን ባይወጉን አይደለም፣ በነጭ ያልተገዛን፣
ተቸግረው እንጂ፣ ስንሞት እየበዛን፡፡


ለቀይ ወንበሯ፤ ለእማሆይ አበቅየለሽ … ለክብራቸው እጅ ነሳሁ፡፡
እናንተም እጅ ንሡ!
ሥም ከመቃብር በላይ ነው፡፡

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *