የማፍረጥረጥ ህጎች

በቻቻ /ABN/

እቅጩን ተናገር እንዲል ያገሬ ሰው።

ተፃፈ ፊቱን ለሚደብቀው ህዝብ።

ㄹㄹㄹㄹ
እግዚአብሄር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው
በአፍንጫውም የህይወት እስትንፋስን እፍ አለበት
ሰውም ህያው ነፍስ ያለው ሆነ።
——መ,ቅ ኦሪት ዘ ፍጥረት——

“ወለቀድ ከረምና በኒ አደም”
የሰውን ልጅ አልቀን ፈጠርነው።
— —ቅዱስ ቁርአን——

ይህ ብሩክ ፍጡር የተከለከለን ሰርቆ ከመብላት
አኳኃኑ በኃላ…………
ሌብነትን የፈለሰፈው የመጀመሪያው ፍጡር በመሆን ቃላባይነቱን “ሃ” በማለት ጀመረ።
ዛፍ ላይ ያለን ፍሬ ዘንጥፎ በማሻመድ ተሽመደመደ።

እንደምን ወደተፈጠረበት መሬት ዝቅ በማለት
አታድርግ የተባለውን ታምኖ በማሰቀጠል
መሬት ይበላው ነገር ትሰጠው ዘንድ የሚያስችለውን አቅም ፈጥሮ መስራት ተሳነውና ሃቀኛ መሆን አቃተው።

የሄዋን ገላ ካምላኩ ቃል እንዴት ላቀበት።

ሌብነቱ።

ስለዚህ አንተ ይህን የምታነበው የሌባ ዘር ነህ ማለት ነው።

ምድር በመምጣቱ ባተረፈው እንደተሞገስክ ሁሉ
ጥፋቱንም ልትጋራ ግድ ይልሃል።

አለም ላይ የተፈጠሩ አብዮቶች ያበረከቱልህን
ቅርስ እያስጎበኘህ ዶላር እንደምትዝቅበት ሁሉ
አለም ላይ ጥለውት የሄዱትን ዳፋ ካሳ ልትከፍልበት
ትገደዳለህ።

አርበኛ አያቶችህ ግፈኛም እንደሆኑ
ፃድቅ እንደሆኑ ሁሉ ኃጥእ እንደሆኑ
ሊቅ እንደሆኑ ሁሉ ልቅ
ጠቢብ እንደሆኑ ሁሉ ጠባብ
መሆናቸውን ተቀበል።

የማፍረጥረጥ ህግ እውነተኛ የአለምን ገፅታ ይገነባል።
እቅጩን።

ስለዚህ አንተ ማለት Half cast ነህ።
የሰውነት ውሃ ልክ
የተመረጠ ዘር ወዘተ የሚለውን ተረተረትህን ትተህ

ሌባም ታማኝም ከሆነ የሰው ዘር የተዳቀልህ መሆንህን
እመን።
እየመረረህም።

እየመረረህ ሲባል ያልሆንከውን ሲጫንብህ
መቀበል ሳይሆን የሆንከውን ባልሆንከው አጣፍተው
የጋቱህን እንድትጥል ሲያስታውሱህ ነው።
ከልምምድህ ሲነጥሉህ።

ይሄ አባታችን አዳም የምንለው የመጀመሪያው ሰው።
እስካንተ ድረስ ያለው።

የብፁእነት ኒሻኑን በወሮበልነት ተክቶ
በቃየልና በአቤል አነሳሽነት ጎጠኝነትን ፈብርኮ
እስከ ኤስማኤልና ይስሃቅ ህዝቦች ተሻግሮ
የአርያንና የአይሁድ ወደሚል የዘር ዘውግ ተፈጥፍጦ
ኦሽዊት ይሉት የመበያያ እና የመፋጃ መጋዘን ፈጥሮ

ይሄው ዘውዳዊና ፌደራሊዝምን ተገን በማድረግ

አደገኛ ቦዘኔ ተብሎ በፌደራል መላእክት ኢትዮጵያ የምትባል ዘብጥያ ውስጥ ተወረወረ።
ሌብነት ሱስ ነውና ሰጋቱራን እንጀራ በማድረግ ሂደት ላይ ተጠመደ።

ይህ”የማፍረጥረጥ ህግ” የሚሰራው ግፍና መሰል
ጥፋቱ እንዳይፀና ባንጎላችን የማቅኛና የማንቂያ ጥበቡን ፈጠርነ።

አትስረቅ የሚለውን ቃል መነሻ አድርገን።

እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር የሚል ብሂል
የፈጠረ ሊቅ ህዝብ ሚዳቋ እያዬ ቀበሮ አየነ ብሎ
ሃሰትን እውነት በማድረግ ህግ ከተስማማ የመሸበት
ባልመሸበት ነው ወይ ወደሚል የራስ መጠይቅ ያሻግራል።

የሃገራችን “እውነትን ተናግሮ የመሸበት የማደር” ባህል
ቀበሮን ሚዳቋ በማድረግ ላይ ስሙሙነት ያለው ነው።

ኢትዮጵያን ሱዳን ነሽ የማለት “ኢ—ሳይንሳዊ”አስተምህሮ።

ቶም & ጀሪ የነባራዊው አለም ድብና ጅብ ናቸው
ብሎ የመለፈፍ ያህል።

ህዝበ ኢትዮጵያንም ለዚህ እኩይ ቃል ጆሮ ሰጥቶ
ሃዋሪያ ሆኖ የመከተል አዝማሚያ ባየንበት ግዜ
የመገሰጫ ቃል ከአምሳለ አስተዋዩ ይቸረው ዘንድ
አፋችንን አሶገግነ።

ማሞጥሞጥ።

ማፍረጥረጥ ከማፈንገጥ ህጎች ይበልጡን ተጋፋጭ ነው።
ማለሳለስ ማስመሰል እና አድር ባይነት አይታይበትም።

ፊትለፊታዊ ፍልስፍና ነው።

“አካፋን አካፋ፣ዶማን ዶማ”

የኢትዮጵያ የ3000 አመት የስልጣኔ ጉዞ ሪፎርሙ
ያልተፋጠነው በማለሳለስ፣በማስመሰል በነውርና
በይሉኝታ ህጎች ታጥሮ ነው።

የግመል ሽንት የሆነ የእድገት ጉዟችን ከዚህ ይጀምራል።

ይህ ደግሞ …………
በዜና መዋእላችን
በንፅፅራችን
በሴራ ፖለቲካችን
በአሰተዳደራዊ ሰርአታችን ውስጥ ሲተገበር ኖሯል።
በጠያቂነት ድፍረት ካናካሽ ባህላችን ውልቅ ብለን
እንድንወጣ
isuzu
Mitsubushi ነው ለሚለን አፋዊ ተራኪ
በሚታይ፣በሚዳሰስና በሚጨበጥ ህግ ፊትለፊት ተጋፍጠን ሊጭንብን ያለውን አይጠቅሜ ትርክት
እሱም እንዳያስቀጥለው በማስጣል ካፍረጥራጭ ህዝቦች ተርታ ልንሰለፍ ይገባል።
ዶማ።
አካፋ።
እያልን………
እዚህ ላይ የመሸነጋገል ወይም በነኪኪ በነ ጆኒ ቋንቋ
የመሞዳሞድ ህጎች አይሰሩም።
እቅጩን።

ይህ ትውልድ በማያውቀው የድሮ ትርክት እየተነዳ
የዛሬ ግዜውን እየተቀማ ይገኛል።
እምቢ ባይ ሆኖ የራሱን አለም ያቀና ዘንድ አፍረጥራጭ መሆን አለበት።

በዘመኑ ብሂል”መስሚያዬ ጥጥ ነው” ይበል።

ተራኪ አባቶች ሰሪ ልጅ አይፈጥሩምና።

እናም cost sharing ያስፈልጋል።
ወጭ መጋራት።

“ወጭ መጋራት” ማለት “የጠፉት ጥፋቶች” በሚል
ተተክቶ ይተርጎም።

ስለዚህ መፃኢውን ትውልድ ለመታደግ ሲባል
አፍረጥራጭ አርጎ የሚያንፅ ካሪክለም በትምህርት ስርአታችን ውስጥ ማካተት ያስፈልጋል።

የራሱን እውነታ ጣይ እና ባላመነበት ላይ አማፂ እንጅ
* ተለማማጭ
* አጎብዳጅ
* ተቀባይ
* ጠባቂ
ዜጋ ለዚህች አለም ሸክም ነው።

ከዚህ በኃላ የማፈንገጥ ጥበቦችን ተጠቅመን
እናፍረጥርጥ።

የጠቢቡ ሶሎሞንን ሊቅነት እንደምናጎላ ሁሉ
የወሲብ ቅሌቱንም እንዲሁ እናውሳ።
የመንግስቱ ኃይለማርያምን አምባገነንነት እንደምንነዛ ሁሉ
ለሃገር የዋለውን ውለታ እናስታውስ።

አሸናፊ ህዝቦች የማይክዱ ናችው።

ከሃዲ ዜጋ እርቦት ያኘከውንም ለመዋጥ ክፈሉኝ ይላል።

አፍረጥርጠን በመንገር
አፍረጥርጦ የሚጠይቅ
አፍረጥርጦ ታሪክ የሚያወርስ ኢትዮጵያዊ በዚች ሃገር
ይኖር ዘንድ ይችን ቁንፅል የመነሻ ሃሳብ የፍልስፍና
አቅጣጫ አሳዬነ።
በቀጣይ በጥልቀት የምንዳስሰው ይሆናል።
ያለያ
ፈጣን wife ሳይሆን
ፈጣን wifi ያለበትን በማሰስ ላይ የተጠመደው
ህዝባችን ዘሩን ተክቶ በስልጡን ዜጋ አገሩን ከመገንባት ይልቅ አሉታዊ ወጎችን እየገነባ አገሩን ያፈርሳል።

ስለዚህ

በአፍላነት ወዝህ እንደጎመራህ ትቆይ ዘንድ
ፍሪጅ ውስጥ የሚከትህ እሱ ከሰው ልጅ የንቃት እድገት
የተገታ ነው።

ፔፕሲ እንደሆንክ ከተሰማው።

ከዝግመትህ ትነቃ ዘንድ ኦቭን ውስጥ ከቶ የሚያበስልህ
እርሱ ውሃ ሽቅብ እንደሚወጣ አስቦ የበዬነ ነው።

ፒዛ እንደሆንክ ከተሰማው።

ሰው ነህና በራስህ የፍጥረት ሂደት ነው የምትፈካው
የምትከስመው።

“Matesbiku min umetin ajeliha
wema yesteehirun”

ማንኛይቱም ህዝብ ግዜዋን ምንም አትቀድምም።
ከእርሷም አይቆዩም።

የዘረመል፣የኢንተረስትና የIQ ሁኔታ አንተን ከሱ የሚለይ
ሆኖ የመገኘት እድል አይኖረውም ብለህ አታስብ።
ምህንያቱም ሰጋቱራ እንጀራ እንዳልሆነ እያሰብህ
እንደ እንጆሪ የሚጣፍጥ ነው እያልህ እያበላህ
እየተበላህ ነው።

ተጣጥሎ በመሂያሂያድ ውስጥ ደግሞ ሰውነት የለም።

ሰው ማለት።

በየራሱ ሁናቴ ቆሞ በየራሱ ዛቢያ የሚቆመውን
የማይገፋ ነው።

ሰው ማለት።
ያለመስፈርት እንዲሁ የሚኃኃን ነው።

ሰው ማለት።

የተፈጥሮን የማይዛነፍ ሂደት ሳይንሳዊ ባልሆን መንገድ
የማይቃረን ነው።

ተመራምሮ ተፈላስፎ የሚገራ።
እንጅ።
ተመራርሮ ወይም ተንፈላስሶ የሚያቅራራ አላልሁም።

ሰው አለማለት ግን………

የአለምን ሁኔታ በማይለውጥ ነገር ላይ የሚባክን ነው።
ለየእለት መቆያው ወይም ካንዱ ቀን ወዳንዱ ቀን
ለመሻገር የሚያስችለው እሳቤ ላይ ሙጥኝ ማለት ነው።

እህላዊ ጉዞ።
ፌንጣዊ አፈጣጠር።

ሰው ሰው አለማለት ከንቱ ነው።

አፍረጥርጥ።

ተለጣፊና ተጣጣፊ ሰው አለመሆንህ ታምኖበት
“እሱ እኮ ለቋል” ከመባል ውጭ የሚለጠፍልህ
ሌላው ስያሜ “እሱ እኮ ነገረ ስራው ግራ ነው”
የሚል ስለሆነ…………

አፍረጥርጥ።

የሚወላውል ህዝብ
የሚያመነታ አለም
የሚፈራ ሃገር አፍራጭ ነው።

ነግሬሃለሁ አገርህ ትነቃ ዘንድ አፍረጥርጥ።

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *