እንኳን ከሴት ጋር ወንድ ከወንድ ጋርም ልዩነት አለው

በተሾመ ፈንታሁን /ABN/

ከሜዳ ውጭ ሲያዩዋት ከፊቷ ፈገግታ የማይለያት ፍልቅልቅና ተጫዋች ናት፡፡ ሜዳ ላይ ደግሞ ኮስታራና ቆራጥ የውሳኔ ሰው፡፡ የአቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ መጽሔት የዚህ ወር እንግዳ አርቢትር ሊዲያ አበበ፡፡  ተወልዳ ያደገችው ጅማ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ሊዲያ በልጅነትዋ ከእግር ኳስ ይልቅ ቅርጫት ኳስ ታዘወትር ነበር፡፡ ባጋጣሚ የገባችበት የእግር ኳስ የዳኝነት ኮርስ ግን ሳታስበው አስጥሟት፤ ዛሬ  በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ሃገራችንን በግንባር ቀደምትነት ከሚወክሉ ጥቂት የእግር ኳስ ዳኞት አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡ በመጪው ወር በፈረንሳይ ሃገር የሚካሄደውን የሴቶች ዓለም ዋንጫ እንዲመሩ ከተመረጡ አፍሪካውያን ዳኞች አንዷ ሊዲያ አበበ ናት፡፡ ሊዲያ ወደ ፈረንሳይ ከማቅናቷ በፊት በተለያዩ ርዕሶች ላይ ተጨዋውተናል መልካም ንባብ፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ በቅድሚያ ስለአስተዳደግሽ አጫውቺን እስቲ …

ሊዲያ፡ ተወልጄ ያደግኩት ጅማ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ስፖርት ውስጥ ብዙ እሳተፍ ነበር፡፡ ቅርጫት ኳስ ኦሮሚያን ወክዬ ተወዳድሬ ነበር፡፡ ሩጫም እግር ኳስም ቅርጫት ኳስም እሳተፍ ነበር፤ ስለዚህ ሁሌም ስፖርቱ ውስጥ ነበርኩ፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ታዲያ በምን አጋጣሚ ከቅርጫት ኳስ ወደእግር ኳስ ዳኝነት ገባሽ?

ሊዲያ፡ ወደዳኝነት የገባሁት ባጋጣሚ ነው፡፡ በወቅቱ የስልጠና ዕድሉ ሲመጣ አራት ልጆች ተመርጠን እንድንካተት ተደረገ፡፡ ስልጠናውን ስወስድ አስተማሪዬ የነበሩት ኢንስትራክተር ሽፈራው ጎበዝ እንደሆንኩ እየነገሩ ያበረታቱኝ ስለነበር በዛው ቀጠልኩ፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ሊዲያን ለዛሬ ማንነቷ ያበቋት ሶስት ነገሮች ….

ሊዲያ፡ ለመማር ሁሌም ቢሆን ዝግጁ ነኝ፤ የሚነግሩኝን በቀላሉ እቀበላለው፡፡ ሕግ ሲነገርህ ለመተንተን መሞከር የለብህም፤ በቀላሉ መቀበል አለብህ፡፡ እኔ ሕግን ለመረዳት በጣም ዝግጁ ነኝ፡፡ ሁለተኛ ሙያዬን በጣም አከብራለው ለሙያዬ በጣም ታማኝ ነኝ፡፡ በመጨረሻ ዳኝነት የሚፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ አደርጋለው፡፡ ስልጠናዎቼን በሥርዓት እፈጽማለው፣ እራሴን እጠብቃለው፣ ሁልጊዜም ለውድድር እንደሚዘጋጅ ስፖርተኛ እዘጋጃለው፣ ሶስተኛ አነባለው፣ ሌሎች ዳኞች ሲያጫውቱ እከታተላለው፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ከወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ጋር በተያያዘ ከፌዴሬሽን ጋር የተፈጠረው ነገር ምንድን ነው?

ሊዲያ፡ ሌላ ሃገራት ከእግር ኳስ ደረጃቸው ጥራት የተነሳ፣ በርግጥ አዲስ ሕግ ባይሆንም ሴቶች ወንዶችን ለማጫወት በወንድ ሩጫ መሮጥ አለባቸው የሚል ሕግ አለ፡፡ ሕጉ ሲወጣ እኔ ወሊድ ላይ ነበርኩና ከዛ ስመለስ ወደቀድሞ ብቃቴ ለመመለስ ብዙ ጥረት አድርጌ በመጨረሻ ወደከፍተኛ ሊግ እንድመለስ ተደረገ፡፡ እኔ አፍሪካ ዋንጫና ዓለም ዋንጫን ካጫወትኩ በኋላ ፕሪሚየር ሊግ እንደማጫውት አስቤ ነበር፡፡ ማንም ሰው ትዳኛለሽ ወይም አትዳኚም አላለኝም ነገር ግን ሁሌም ከምደባ ውጭ እሆን ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ሁሌም እንደምመለስ አውቅ ነበር፡፡

ሌሎች ሃገራት ሴቶችን በወንድ ሰዓት አይደለም የሚፈትኗቸው የራሳቸው ሰዓት አላቸው፡፡ ወንዶችና ሴቶች በተመሳሳይ ሰዓት ሲፈተኑ መጠነኛ ልዩነት መታየቱ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የእንግሊዝና የስፔን ሊግ ላይ እንኳን ስታይ አንዳንድ ጊዜ እውነት እነዚ ዳኞች ኩፐር ቴስት ተፈትነው ነው ትላለህ፡፡ የሊጎቹንም ደረጃ ከግምት ማስገባት ደግሞ አለብህ፡፡ የኛን ተጫዋቾች ፍጥነትና አቅም ከእግሊዝ ሊግ ተጫዋቾች ጋር ለማነጻጸር በፍጹም አይቻልም፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ሌላ ሃገራት ለዓለም ዋንጫ የተጠሩ ዳኞችን በፊፋ ጣልቃ ገብነት ሲያበረታቱ ይታያል ለምሳሌ ስቴፋኒ ፍራፓር የምትባለው ፈረንሳያዊት ዳኛ በፊፋ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ሊግ 1 ላይ እንድታጫውት ተደርጓል ፊፋ በኛ ሃገር ፌዴሬሽን ላይ ወይም የኛ ፌዴሬሽን አንቺ በብቃትሽ ላይ እንድትቆዪ የተደረገ ጥረት ካለ?

ሊዲያ፡ እኔም ስል የነበረው ይህንኑ ነው፡፡ ባምላክ በሚሮጥበት ሰዓትነው አንድ ፌዴራል ዳኛ የሚፈተነው፡፡ እንኳን ከሴት ጋር ወንድ ከወንድ ጋርም ልዩነት አለው፡፡ እኔ ይህን ሰዓት ለሟላው እችላለው፡፡ ሌሎች ከኔ በኋላ የሚመጡ ታዳጊዎች ግን ለምን ይሰቃያሉ፡፡ ለዛ ነው ስታገል የነበረው፡፡ ስቴፋኒ በፊፋ ተጽዕኖ አጫወተች፡፡ ሌላም ብዙ ሃገራት ለሴት ዳኞቻቸው ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ፊፋ ለሌሎች ሃገራት ደብዳቤ ሲልክ ለኛም ፌዴሬሽን ልኳል፡፡ ፊፋ የጻፈው ደብዳቤ ላይ ሊዲያ የሀገሪቱን ትልቁን ሊግ ማጫወት አለባት ይላል፡፡ ነገር ግን የፌዴሬሽን ሰዎች ደብዳቤ አይተው መልስ አይጽፉም፡፡ እንደውም የፊፋ ሰዎች ያንቺ ፌዴሬሽን ደብዳቤ እንኳን አይመልስም ይሉኛል፡፡ እንኳን ለፊፋ ለኔም በግልጽ ማጫወት አትችዪም ወይም ትችያለሽ ያለኝ ሰው የለም፡፡ ይታያል፣ እናየዋለን…….

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ስትመለሺም ትልልቅ ጨዋታዎች ላይ ነው እንድትመለሺ የተደረገው…..

ሊዲያ፡ የተመለስኩበት ጨዋታ በርግጥም ማጫወት እንደምችል ያሳየሁበት ጨዋታ ነው፡፡ በቴሌቪዥንም ስለተላለፈ ብዙ ሰው አይቶታል፡፡ ሰዉም ከዛ በፊት በሚዲያ ይነገር ስለነበር ከጨዋታው እኩል የኔን ጉዳይ ጠብቆት ነበር፤ ጥሩ ጨዋታ ነበር፡፡ እኔ ለኔ ብቻ አይደለም የምታገለው ከኔ በኋላ ለሚመጡ ብዙ ታዳጊዎችም እንጂ፡፡ እኔ ተቀብዬ ዳኝነት ባቆም ከኔ በኋላ የሚመጡ ታዳጊዎች ላይኖሩ ይችላሉ፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ እንደው ግን የፌዴሬሽን ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላሉ ብለሽ ታስቢያለሽ?

ሊዲያ፡ በጣም የሚገርመው ለሊዲያ ብንሰጥ ሌሎችም ሴት ዳኖች ይጠይቃሉ ብለው ሁሉ ይሰጋሉ፡፡ ለምሳሌ ፈረንሳይ ሁለት ዳኞችን ለዓለም ዋንጫ አስመርጣለች፤ ሰቴፋኒና ኢማኑኤላ (የመስመር ዳኛ ናት)፡፡ ስቴፋኒ ሁለተኛ ሊግ ስታጫውት ኢማኑኤላ ደግሞ ሶስተኛ ሊግ ነው ስታጫውት የነበረው፡፡ ኢማኑኤላ እንዴት ብላ አትጠይቅም፡፡ እኛጋም ባጅ የሌላቸው፣ ኢንተርናሽናል ባጅ ያለጠፉ ዳኞች ይጠይቃሉ ብለህ የሚችል ሰው አትገፋም በዳኞች መካከል ያለ ልዩነት ሊበረታታ ነው የሚገባው፡፡ እንደማወዳደሪያ ልትገለገልበት ሁሉ ይገባል፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ሪቪው፡ ዓለም ዋንጫ እንደተመረጥሽ ስታውቂ ምን ተሰማሽ?

ሊዲያ፡ ዝግጅት የጀመርነው በ2016 እ.ኤ.አ. ነው፡፡ ከአፍሪካ አስር ዳኖች ተመርጠን ካታር ለዝግጅት ተላክን፡፡ ከዝግጅት በኋላ በነበረ ምዘና ስድስት ቀረን፡፡ ከዛም ወደኣራት በመጨረሻ ሁለት የመሃል ዳኞች እና አንድ አራተኛ ዳኛ ከሩዋንዳ አብራን ትጓዛለች እና አዲስ አይደለም እንደምሄድ ካወቅኩ ቆየት ብያለው፡፡ ፈረንሳይ ለከ20ዓመት በታች ውድድር ስሄድ ለዓለም ዋንጫ እንደምሄድ አውቀው ነበር፡፡ በውድድሩ ላይ የሚኖረኝ ሚናም መሃል ዳኝነት ነው፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ለዓለም ዋንጫ ዝግጅትሽ እንዴት ነው?

ሊዲያ፡ ችግሬን እኔም አውቀዋለው፤ እነሱም ያውቁታል፡፡ ኢትዮጵያውያን ዳኞች ፍጥነትና ጥንካሬ ይጎላችኋል ይሉኛል፡፡ ለካታር የመጨረሻ ፈተና ስዘጋጅ የማረሚያ ቤትን የአጭር ርቀት አሰልጣኝ ይዤ ነበር እዘጋጅ የነበረው፡፡ ተመልሼ ለፈተና ስሄድ 40 ማይክሮ ሰከንድ ቀንሼ ሲያኙን በጣም ነበር የገረማቸው፡፡ አሁንም ሚያዝያ ላይ ለመጨረሻ ፈተና ስሄድ ሰውነቴን ቀንሼ ነው ያገኙን በሱም በጣም ደስተኛ ናቸው፤ እንደዚ ሆነሽ ነው ልናይሽ የምንፈልገው ነው ያሉኝ፡፡ እኔ ተግዳሮት አልጠላም የባሰ እንድነሳሳ ነው የሚያደርገኝ፡፡ ዕድሎችንም በአግባቡ ነው የምጠቀመው፡፡ ጠንክሬ እሰራለው እግዚአብሄርም ይረዳኛል፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ የአፍሪካ፣ የዓለም ዋንጫዎችን መርተሻል፡፡ የታዳጊና የወጣት ውድድሮችንም አጫውተሻል፡፡ ከማቆምሽ በፊት ይሄ ይቀረኛል የምትዪውና ሳታደርጊው ብትቀሪ የሚጸጽትሽ፡፡ ይህ ቀረኝ የምትዪው ነገር?

ሊዲያ፡ 4 የአፍሪካ ዋንጫ፣ 2 የዓለም ዋንጫ፣ ከ17ዓመት በታች የአፍሪካም የዓለምም ዋንጫ፣ ከ20ዓመት በታች የአፍሪካም የዓለምም ዋንጫ አጫውቻለው፡፡ ስጀምርም ይሄን ያህል ለመሄድ ነበር ህልሜ፡፡

ሕልሜ ተሳክቷል፤ አሁን መቀጠል አለመቀጠሌን ከዓለም ዋንጫው ስመለስ እወስናለው ነገር ግን ታላቁ ውድድር የኦሎምፒክ ውድድር ነውና የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ባጫውት ደስ ይለኝ ነበር፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ለሴት ዳኞች በተለይ ለሴቶች በአጠቃላይ የምትመክሪያቸው

ሊዲያ፡ ምንም ነገር ሲደርስብኝ ሴት ስለሆንኩ ነው የደረሰብኝ ብዬ በፍጹም አላሳብም፡፡ ማንኛውም ወንድ ዳኛ ላይ የሚደርስ ነው ብዬ ነው የማስብም፡፡ ወንድ ዳኞች ጠዋት ልምምድ ሰርተው ወደሥራ የሚሄዱት እኔ ቀኑን ሙሉ ጊዜ ስላለኝ በኋላ እሰራለው አልልም ተነስቼ አብሬ ሰርቼ እነሱ ወደሥራ ሲሄዴ እኔም ወደጉዳዬ እሄዳለው፡፡ ከጎደለብኝ ይልቅ ያለኝ ነገር ላይ ነው ማተኮር የምፈልገው፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ሪቪው፡ ይሄን ሁሉ ልምድ በመጨረሻ በመጽሓፍ ሰንዶ የማቆየት ሃሳብ

ሊዲያ፡ አዎን ብዙ ሰዎች ይሉኛል በመጨረሻ ሳቆም ስንብቴ የሚሆነው በሱ ነው፤ መጽሃፍ መጻፌ አይቀርም፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ስለ VAR ምንድን ነው የምታስቢው?

ሊዲያ፡ ዳኛ ዘጠናውን ደቂቃ ያለስህተት ሊሰራ አይችልም፣ ሰው ነው ይሳሳታል፡፡ ስለዚህ ቫር ያርመዋል፣ ያግዘዋል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ምናልባት ያስተማረኝ ኮሊና ስለሆነ ሊሆን ይችላል፤ ለቫር ፖሲቲቭ አመለካከት ነው ያለኝ፡፡ ሰው ነኝ ላላይ፣ወይም ልሳሳት እችላለው ስለዚህ ቴክኖሎጂው ሊያግዘኝ እንጂ እንቅፋ ሊሆን አልተፈጠረም ብዬ ነው የማስበው፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ስለዚህ የምታደንቂው ዳኛ ኮሊና ነው ማለት ነው?

ሊዲያ፡ ኮሊናና ማሲሞ ቡሳካን በጣም የመወዳቸው ዳኞች ናቸው፡፡ በዳኝነት ኮሊና አንደኛ ነው፡፡ ማሲሞ ደግሞ የሚገርም አሰልጣኝና የሚያስደንቅ መምህር ነው፡፡ ለሁለቱም እጅግ የበዛ ክብር አለኝ፤ በነሱ መሰልጠን ደግሞ ዕድለኝነት ነው፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ በትርፍ ጊዜዋ ሊዲያ ምን ታደርጋለች?

ሊዲያ፡ ኳስ ቀጥታ ማየት እወዳለው፣ ስታዲየም አልቀርም፡፡ ኳሶችንም በቴሌቪዥን አያለው፤ የራሴንም ሌላውንም አያለው፣ አነባለው፣ ከቤተሰብና ከጓደኞቼ ጋራ እዝናናለው፡፡ አሁን ደግሞ ያለም ዋንጫ ዝግጅት ስለሆነ ብዙ ሪፖርቶች እጽፋለው፣ ማሳጅ አደርጋለው ብዙውን ሰዓት በዝግጅት ነው የማሳልፈው፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ዳኝነት ካቆምሽ በኋላስ …?

ሊዲያ፡ ጥሩ ኢንስትራክተር መሆን እፈልጋለው፣ ያለፍኩበትን ሁሉ ማስተማር ነው የመጀመሪያ እቅዴ፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ እኛ ሃገር አራተኛ ዳኝነት ላይ አፈጻጸም ችግር የለም ዋናው አሰልጣኝ መምከሪያ ቦታው ላይ ሆኖ ሁለቱም ይጮሃሉ የቡድን መሪው ዋና አሰልጣኙን ይመክራል አንዳንድ ጊዜ አራቱም ያቆማሉ አራተኛ ዳኛን ይከባሉ አራተኛ ዳኛ ስልጣኑ እስከምን ድረስ ነው?

ሊዲያ፡ እኛ ሃገር ማጫወት በጣም ከባድ ነው፡፡ አሰልጣኝ ማሰልጠኑን ትቶ ዳኛ ይገመግማል፣ ተጫዋች ዳኛን ይገመግማል፣ ደጋፊ ዳኛን ይገመግማል፤ በጣም ከባድ ነው፡፡ እውነት ነው ዳኛም ጋር ችግር አለ፡፡ ችግር ሲኖር ግን በሥርዓት ነው ሊጠይቅህና ሊያናግርህ የሚገባው፤ እያመናጨቀህ፣ እያሳጥህ፣ እየሰደበህ መሆን የለበትም፡፡ አራተኛ ዳኞች አስተዳደራዊ ሥራዎች ላይ ሙሉ ስልጣን አለው፡፡ ዳኛ ጠርቶ ማስቀጣት ይችላል፤ እኛ ሃገር ግን መተዛዘኑ አለ፣ መፈራራቱም አለ፡፡ አራተኛ ዳኛ መሃል ዳኛን ከጠራ የመጨረሻ ውሳኔ ነው የሚሆነው ስለዚህ አራተኛው ዳኛ ብዙ ጊዜ የመሃል ዳኛውን አይጠራም፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ስለቤተሰብሽ ….?

ሊዲያ፡ ሞገስ የሆነች ሴት ልጅ አለችኝ፤ ሶሊያና ትባላለች፡፡ ስድስት ዓመቷ ነው፡፡ ሥርዓት ያላት ልጅ ናት፡፡ እኔም ኣባቷም ውጭ ነው የምንውለው ነገርግን ወላጆቿ ውጭ እንደምንውል ሳይሆን በጣም ሥርዓት ያላት ልጅ ናት፤ ትረዳናለች፡፡ አብረና እንደማነውል አይደለችም በሥራችን ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖ አታሳድርም፣ ከዓለም ዋንጫው በኋላ ደግሞ እንደእግዚአብሔር ፍቃድ ሶሊያና እህት ወይ ወንድም ይኖራታል ማለት ነው፡፡ ሶሊያናን ከወለድኩ በኋላ በርካታ ጥሩ ነገሮችን በሕይወቴ አይቻለው፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ በመጨረሻ ማመስገን የምትፈልጊው ወይም መናገር የምትፈልጊው ነገር ካለ፣ ይኸው …..

ሊዲያ፡ እኔን ለዚ ያበቁኝ፤ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ በመጀመሪያ በሥልጠና፣ ያስተማሩኝ፤ ከዛም በሥራ ፌዴሬሽን ያሉ አመራሮች፣ የኮሚቴ አመራሮች፣ የሙያ ባልደረቦቼ በሙሉ፡፡ የእኔ እዚ መድረስ የሚያስደስተው፤ የኔም ብቻ ሳይሆን ሴት ዳኞች የተሻለ ቦታ እንዲደርሱ ሁሌም ሆን በቅንነት የሚያግዝ ቅን ሰው አቶ ፀሃዬ ገብረእግዚአብሄር፡፡ በዳኝነት ያለሳለፈ፣ ነገርግን ለዳኞች የተለየ ሰው የነበረ ሰው ነው፤ እሱን ማመስገን ይገባል፡፡ አስተማሪዬ ኢንስትራክተር ሽፈራው፣ ሌሎች ኢንስትራክተሮች በሙሉ፣ ጓደኞቼ፣ አብረውኝ ልምምድ የሚያደርጉ ዳኞች፣ በሙሉ የኢትዮጵያ ዳኞች፣ ባጠቃላይ የስፖርት ኅብረተሰብ፣ ደጋፊዎች በሙሉ፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ ቤተሰቦቼን፣ ባለቤቴን፣ ልጄን በሙሉ ስማቸውን ያልጠቀስኩት ብዙ ወዳጆቼ በሙሉ አመሰግናለው፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ፈቃደኛ ሆነሽ ቃለመጠይቁን ስለጠቀበልሽ፣ በጣም ከተጣበበ ጊዜሽ ላይ ይህን ሁሉ ሰዓት ሰጥተሸ ጥያቄዎቼን ስለመለስሽ በአንባቢዎች ስም ከልብ አመሰግናለው፡፡

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *