አመለ ሸጋው ፡መሱድ መሃመድ

በተሾመ ፋንታሁን

ABN#

ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ቄራ አካባቢ ነው፡፡ አልማዝዬ ሜዳ ተጫውቶ ካደገ በኋላ የመብራት ኃይልን ታዳጊ ቡድን ተቀላቀለ፡፡ ፕሮፌሽናል እግር ኳስን የጀመረው በመብራት ኃይል እሁን እንጂ አብዛኛውን የእግር ኳስ ዘመኑን ያሳለፈው ግን በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ነው፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና አምበል ጫማውን በኢትዮጵያ ቡና ሰቅላል ተብሎ ሲጠበቅ ሳይታሰብ የጅማ አባጅፋርን ክለብ ተቀላቀለ፡፡ አመለ ሸጋው፣ ያሁኑ የጅማ ጅፋር አምበል የኢትዮጵያ ቡና ምልክት መሱድ መሃመድ ከABN የስፖርት አዘጋጅ ተሾመ ፋንታሁን ጋር ቆይታ አድርጓል፤ መልካም ንባብ፡፡

ዘንድሮ በሁለቱም አህጉራዊ ውድድሮች፡ በሻምፒዮንስ ሊግም በኮንፌዴሬሽን ዋንጫም ተሳታፊ ነበራችሁ፤ ከአዲሱ ክለብህ ጋር አህጉራዊ ጉዟችሁ ምን ይመስል ነበር?

ጅማ አባጅፋር ለአህጉራዊ ውድድር አዲስ ነው፡፡ ክለቡ እንደአዲስነቱ መጥፎ የውድድር ጊዜ አሳልፏል ብዬ አላስብም፡፡ በቡድንም ይሁን በተናጠል ሁላችንም ጥሩ ልምድና ትምህርት አግኝተንበታል፡፡

እኔ በግሌ ለውድድሮቹ አዲስ አይደለሁም፤ ከቡና ጋር ከአልአህሊ ጋር ተጫውቻለው፡፡ እኔም ብቻ ሳልሆን ሌሎች የሻምፒዮንስ ሊግና የኮንፌዴሬሽን ጨዋታ ያደረጉ ልጆች በክለባችን አሉ፡፡ ነገር ግን የሻምፒዮንስ ሊግም ሆነ የኮንፌዴሬሽን ውድድሮች የየሃገሩን ሻምፒዮን ቡድኖች የሚያሳትፉ ውድድሮች እንደመሆናቸው ደረጃቸው ከፍ ያለ ደረጃቸው ከፍ ያለ ውድድሮች ናቸው፡፡ እናም ሁሌም ቢሆን አዲስና ከባድ ውድድሮች ናቸው፡፡ ሁሉም ቡድን እያደገ፣ እየተሻሻለ የሚመጣባቸው ውድድሮች ስለሆኑ ጨዋታዎቹ ሁሌም ከባድ ናቸው፡፡

ያደግከው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ታዳጊ ቡድን ነው፤ ከዛም ኢጥዮጵያ ቡና ገባህ፡፡ ረዥሙን የጨዋታ ጊዜህን ያሳለፍከው ኢትዮጵያ ቡና ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቡና ጫማ ትሰቅላለህ ተብለህ ስትጠበቅ ወደጅማ አባጅፋር አቀናህ፡፡ ከኢትዮጵያ ቡና የተለየ ማሊያ በተለይ ደግሞ የክልል ክለብ የተለየ ስሜት አለው?

እኔ እንዳልከው ብዙውን ጊዜዬን ያሳለፍኩት በቡና ገበያ ነው፡፡አንድ ክለብ ውስጥ ብዙ መቆየት አንተንም እንድትረጋጋ ያደርግሃል በቡድኑም ተጫዋቾች መሃል የባለቤትነትን መንፈስ ይፈጥራል፡፡ ቡና ውስጥ እየነበርኩ ከአሰልጣኞች፣ ከደጋፊው ባጠቃላይ ከክለቡ ቤተሰቦች የተማርኩት ይሄን ነው፡፡ ከአዲስ አበባ መውጣት  በተለይ እንደኔ አዲስ ቤተሰብ ለመሰረተ ሰው በጣም ከባድ ነው፡፡

ለቅድመ-ውድድር ወይም ለጨዋታ የተወሰኑ ቀናትን ነበር የምወጣው ክለብ ቀይሬ ሙሉ ኑሮዬን ጅማ ሳደርግ ቤተሰቦቼ፣ ህጻናት ልጆቼ፣ ባለቤቴ ሁላችንም ነን የተቸገርነው፡፡ በተለይ መጀመሪያ ላይ በጣም ነበር የከበደኝ አሁን ግን እየለመድኩት ነው፡፡

መሱድ የቡና ምልክት ነው፡፡ 3 ቁጥር ቡናና መሱድ ጥብቅ ቁርኝት ነበራቸው፡፡ ቡናን ስትለቅ የተለየ ስሜት ተሰማህ?

እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ እንደምወጣ አላውቅም ነበር፡፡ ከክለቡ ውጭ የሆኑ ቀድመው የሰሙ ሰዎች ደውለው ሲነግሩኝ አላመንኩም ነበር፡፡ የ2010 ዓ.ም. የውድድር ወቅት ማጠናቀቂያ የመዝጊያ በዓል ሲደረግ አብዛኞቹ ውላቸው ያለቀ ልጆች አልተገኙም ነበር፤ እኔ ግን ተገኝቻለው፡፡ ተገኝቼም ግን አልሰማውም ነበር፡፡ ቡና ለኔ ቤቴ ነው፡፡ ረዥም ጊዜ ነው የቆየሁት፡፡ ስለዚህ የሆነው ሁሉ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ ቀድሜ ባውቅ፣ ብሰማ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ከሰማው በኋላ ግን በጣም ባዝንም መጫወት ስላለብኝ የሌሎችን ክለቦች ጥሪ ማስተዋል ጀመርኩ፡፡ የጅማ ጥያቄ ይበልጥ ሳበኝ፣ ተነጋገርን፣ ተስማማን ፈረምኩ ማለት ነው፡፡

አሰልጣኙ በተደጋጋሚ ላንተ ያላቸውን ክብር ከመግለጽ ባሻገር አብረሃቸው እንድትሰራ ጠይቀውህ እንደነበረ ይገልጻሉ ቡና ውስጥ ቆይተህ ረዳ አሰልጣኝ እንድትሆን ጠይቀውህ ነበር?

ዲዲዬ ጎሜስ በውድድሩ አጋማሽ አካባቢ በስልጠና ወቅት የመጪው ዓመት ዕቅዳቸው ውስጥ እንዳለው ነግረውኝ ነበር፡፡ እኔም ከሳቸው ጋር መስራት ደስ እንደሚለኝ ነግሬያቸው ነበር፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ሃሳባቸውን ቀይረው ረዳት አሰልጣኝ እንድሆን ጠየቁኝ ከባድ ውሳኔ ስለነበር ዝም አልኳቸው፡፡ በርግጥም ከባድ ውሳኔ ነበር፡፡ ከዛ ከኔ ምንም ዓይነት መልስ ባልተሰማበት ሁኔታ  ነው ክለቡ ከኔ ጋር ለመለያየት የወሰነው፡፡ አሰልጣኑ ሲነግሩኝ ወዲያው ይቀበለናል ብለው ያሰቡ ይመስለኛል፡፡ ከዛ ድጋሚም አላወራንም በዛ ሁኔታ ክለቡ ውሌ እንደማይታደስ አሳወቀኝ፡፡

ኢትዮጵያ ቡና አንተን ጨምሮ በዛ ያሉ ነባር ተጫዋቾችችን ነው የለቀቀው፡፡ ቡድኑ ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ደህና ቢመስልም እየቆየ ግን በሜዳው ሳይቀር በተደጋጋሚ የሚሸነፍ ቡድን ሆነ፣ የዘንድሮው የኢትዮጵያ ቡና ችግር ምን ይመስልሃል?

 እኔ እንደማስበው ሽግግሩ ልክ አልነበረም፡፡ በአንድ ጊዜ አዲስ ቡድን ነው ለመገንባት የተሞከረው፡፡ በርግጥ ቡና ቤት የተጫዋቾች አንድ ላይ መውጣት የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን ያሁኑን ልዩ የሚያደርገው ሙሉ ለሙሉ ቡድኑ ነው የተለወጠው፡፡ የተወሰኑ ነባር ተጫዋቾችን ትይዛለህ ከአዳዲሶቹ ጋር በማቀናጀት የቡድኑን መንፈስ ለማቆየት ትሞክራለህ ይህ ቢሆን በጣም ጥሩ ነበር፡፡

አሁን የተፈጠረው ነገር ታዳጊዎቹ ጥሩ ናቸው ነገር ግን አንድ ጨዋታ ሲሸነፉ የዓለም መጨረሻ ነው የሚመስላቸው፡፡ እኛም ታዳጊ ሆነን ተጫውተናል እናውቀዋለን፡፡ ዛሬ ብትሸነፍ ነገ እንደምታሸንፍ ታውቀዋለህ፡፡ ይህንን የምትማረው ከአሰልጣኝ አይደለም ከዕድሜ ነው፡፡ ነባር ተጫዋቾች ቢኖሩ ይህን ለልጆቹ እያስረዱልህ ብትሸነፍ እንኳን  ለቀጣይ ጨዋታ እየተዘጋጀህ ውጤትን መቀየር ትችላለህ፡፡

ብዙ ሰው ግን የዘንድሮ ችግር የመሱድ መሃመድ መውጣት ነው ቡድኑ መሪ ነው ያጣው ይላሉ፡፡ አንተ በዚህ ትስማማለህ?

እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም ነባር ተጫዋቾች ቡድኑን በራሳቸው መንገድ ሲጠቅሙ ነበር፡፡ እግር ኳስ የቡድን ውድድር ነው የምታሸንፈውም የምትሸነፈውም በቡድን ነው፡፡ በተለይ እንደዚህ ዓይነት ተከታታይ ሽንፈት በሚመጣበት ጊዜ መረዳዳት አለብህ፡፡ እንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ጊዜያትን ለመሻገር ልምድ ያስፈልግሃል፡፡  ይህን የምትረዳው በቆይታ ነው፡፡ በቡድኑ ውስጥ የተፈጠረው  ነገር ይሄ ይመስለኛል፡፡ ልጆቹ ተረጋግተው በሁለተኛው ዙር የተሻለ ነገር ይሰራሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡

አሰልጣኙም ቢሆን መሱድን መልቀቅ እንዳልነበረባቸው አምነዋል?

እኔ እንደዕድል ሆኖ አምበል ከሆንኩበት ጊዜ ጀምሮ ልጆቹ ያከብሩኛል፣ ይሰሙኛል፡፡ በተለይ አምና ደግሞ ብዙ አዳዲስና ታዳጊ ልጆች ስለነበሩ በቡድኑ ውስጥ መከባበር ነበር፡፡ ልጆቹ ስለሚሰሙኝ እንደትልቅ ተጫዋችም እንደታላቅ ወንድምም ያከብሩኝና ይሰሙኝ ነበር፡፡ እኔም ይሄን ተሰሚነት በመጠቀም በአሰልጣኙና በተጫዋቾች መካከል ድልድይ ሆኜ የበኩሌን ለማድረግ እሞክር ነበር ምናልባት ለዚህ ሊሆን ይችላሉ፡፡

የዘንድሮው የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ዙር ተጠናቋል፡፡ በተለይ እናንተ ሁለት አህጉራዊ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ነበራችሁ፡፡ አንተ የመጀመሪያውን ዙር እንዴት ትገመግመዋለህ?

የውጭ ቸዋታዎችን ጨምሮ ብዙ ጨዋታዎችን አድርገናል በጣም አድካሚ ጉዞዎችን አድርገናል፡፡ በተለይ የሞሮኮው ጉዞ በጣም አድካሚ ነበር፡፡ ከግብጽና ከሞሮኮ ክለቦች ጋር ያደረግናቸው ጨዋታዎች ጉልበት የሚጨርሱ ከባድ ጨዋታዎች ነበሩ፤ በአዕምሮም በጉልበትም ብዙ የተፈትንባቸው ጨዋታዎች ነበሩ፡፡ መጨረሻው አካባቢም ብዙ ቀሪ ጨዋታዎች ስለነበሩብን ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን አድርገናል፡፡ በጣም ደክሞን ነበር፡፡ አሁን እረፍቱ በተለይ ለኛ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በሚገባ አርፈን ጉልበት ሰብስበን እንመለሳለን፡፡

አሰልጣኙ አሁን ተባረዋል መሰናበታቸውን ስትሰማ ምን ተሰማህ?

አዝኛለው ማንኛውም የቡና ስሜት እንዳለው ሰው አዝኛለው አሰልጣኙ በጣም ጎበዝ አሰልጣኝ ናቸው መጀመሪያ እንደሰማው ማመን አቅቶኝ ነበር ይሄን ለሳቸውም ቢሆን በጽሁም መልዕክት ገልጬላቸዋለው፡፡ እራሳቸው መርጠው ያዘጋጁት ቡድን ስለሆነ በዚህ ፍጥነት እነደዚህ ዓይነት ተከታታይ ሽንፈት ይገጥመዋል ብዬ አልገመትኩም ነበር፡፡ እንደሰውም አብሯቸው እንደሰራ ተጫዋችም በጣም ነው ያዘንኩት

እንደአሰልጣኝ ምን ዓይነት አሰልጣኝ ነበሩ?

እኔ እንደመጡ ለሚዲያም ገልጬ ነበር በጣም ጎበዝ አሰልጣኝ ናቸው ቢሚዲያ ብቻ የምናውቃቸውን የእግር ኳስ ቃላት፣ ፍልስፍናዎችና ታክቲኮች ለኛ በቅርብ ያስተማሩን ባለሙያ ናቸው፡፡ ሁሉም አብሯቸው የሰራ በክለቡ ያሉትም የወጡትም ሁሉ የሚመሰክሩት ነው፡፡ ስልጠናቸው በጣም ጥሩ ነው፡፡ ዲዲዬ ጎሜስ ለኔ ምርጥ አሰልጣኝ ናቸው፡፡

ጅማ አባጅፋር ዘንድሮ ብዙ በአህጉራዊ ጉዞዎች ላይ ከመጓጓዣ ትኬት፣ ከተጫዋች ደሞዝ ጋር በተያያዘ ብዙ ችግር እንሰማለን በአህጉራዊ ጉዟችሁ አንዱ ችግር የክለቡ አስተዳደር ችግር እንደሆነ ይነገራል ምንድን ነው ያለው ችግር?

ቡድኑ እንደምታውቀው አዲስ ቡድን ነው፡፡ ከብሄራዊ ሊግ እነደመጣ ሳይታሰብ ሻምፒዮን ሆነ፤ ከዛም በሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ሆነ፡፡ ስኬቶቹ ክለቡን ላልታሰቡ ተጫማሪ ወጪዎች ዳርገውታል፡፡ አፍረካዊ ውድድር ላይ ተሳታፊ መሆኑ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን እንዲያመጣ አስገደደው አዲስ የገቡት ተጫዋቾች የክለቡን የደሞዝ ወጪ ከፍ አደረገው፡፡ ጅማ ደግሞ እንደ አዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር ወዘተ ትልልቅ ግብር ከፋይ ተቋማት ያሏት ከተማ አይደለችም፡፡ የክለቡ ወጪ ሳይታሰበ ነው ያደገው፡፡ የትራንስፖርት ወጪው ያልተጠበቀ ነው፣ ሞሮኮ ሩቅ ነው ወጪውም ብዙ ነው ይህንን ቀድመው ልታስብ አትችልም ዕጣ ነው፡፡ ስለዚህ ሻምፒዮን መሆኑ በአፍሪካ ውድድር ተሳታፊ መሆኑ ድንገት የሆኑ ስለሆኑ ክለቡን ለተጨማሪ ወጪ ዳርገውታል፡፡ የክለቡ አስተዳደር ቀን ከሌት ሰርተው አስተካክለውታል ይሄን የምነግርህ በየቀኑ ስለማያቸው ነው በጣም ጠንካራ አስተዳደር ነው ያለው ስለዚህም ነው ወዲያው ማስተካከል የተቻለው፡፡  

ስለቤተሰብህ ንገረን እስቲ?

ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነኝ፡፡ ሃይመንና ኢያድ የሚባሉ ሁለት ልጆች አሉኝ፡፡ አሁን ከናታቸው ጋር ናቸው፡፡ ባለቤቴ ብቻዋን ነው የምትንከባከባቸው፡፡ አዲስ ቤተሰብ እንደመሆኑ ከቤተሰብ ተለይቼ መኖር በጣም ከባድ ነው፡፡

በተለይ እኔ ደግሞ ሁሉንም ነገር አውጥቼ የመናገር ተፈጥሮ ስለሌለኝ በጣም ነበር ያስቸገረኝ ልጆቼ በጣም ይናፍቁኝ ነበር፡፡ ብቻዬን የማለቅስበት ጊዜ ሁሉ ነበር፡፡ በተለይ ትልቁ በጣም ያስቸግር ነበር አባቴ ለምን አይመጣም ይላል ሥራ ላይ ለው አይመስለውም፡፡ በጣም አስቸጋሪ ስድስት ወራትን ነው ያሳለፍኩት፡፡

ወደፊት ምን እያሰብክ ነው ምናልባት አሰልጣኝ የመሆን ሃሳብ፣ ዝግጅት አለ?

አሁን ሙሉ በሙሉ ትኩረቴ መጫወቱ ላይ ነው፡፡ ጨዋታ ካቆምኩ በኋላ ግን አላውቅም አሰልጣኝነት በመሰረቱ በጣም ከባድ ሙያ ነው ብዙ መማር ማንበብ ይጠይቃል ስለዚህ መጀመሪያ መማርን ማንበብን አስቀድማለው አስፈላጊውን ዕውቀት ከሰበሰብኩ በኋላ ግን ብቁ ነኝ ብዬ ሳምን አሰልጣኝ ልሆን እችላለው

በመጨረሻ ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ካለ

ቤተሰቦቼ ተረድተውኝ ሁሌም ከጎኔ ስለሆኑ አመሰግናለው፣ በኤሌክትሪክ፣ በቡና በነበርኩበት ጊዜ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች ሁሉንም አመሰግናለው፣ የቡና ደጋፊዎችን አመሰግናለው፣ አሁንም በጅማ ደጋፊዎች ለኔ ያላቸው ክብር ምስጋና ያስፈልገዋል፣ የጅማን አሰልጣኞች፣ አመራሮች የክለብ ጓደኞቼን ሁሉንም አመሰግናለው፣ አቢሲኒያንም፣ አንተንም ለግብዣው አመሰግናለው፡፡

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *