ሃገር ከሁሉም ነገር ይቀድማል

በተሾመ ፈንታሁን /ABN/

እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1987 ዓ.ም. በማላቫ ኬንያ ተወለደ፡፡ እንደአብዛኛው አፍሪካዊ ህጻን እግር ኳስን መጀመሪያ በሰፈር፣ ከዚያም በትምህርት ቤት ከፍ ሲልም በክለብ ተጫውቶ የሃገሩን የኬንያን ብሔራዊ ቡድን ግብ ለመጠበቅ በቃ፡፡ ሃገሩ ኬንያ ከ15 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ስትበቃ ቁጥር 1 ተመራጭ ሆኖ በሁሉም የማጣሪያ ጨዋታዎች ተሰልፎ የሃገሩን ግብ ጠብቋል፡፡ የዚህ ወር እንግዳችን የቅዱስ ጊዮርጊስና የኬንያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ሙሶትሲ ማታሲ ነው፣ መልካም ንባብ፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ በቅድሚያ ስለአስተዳደግህ ስለተጫወትክባቸው ክለቦች ንገረን

ማታሲ፡ እንደአብዛኛው አፍሪካዊ ህጻን እግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት ከሰፈር ነው፣ ከዛም በትምህርት ቤት፣ ከፍ ስልም በትምህርት ቤቴ አቅራቢያ ይገኝ ለነበረው ምዕራብ ኬንያ ስኳር ፋብሪካ ከዛም  ኤ.ኤፍ.ሲ ሌኦፓርድስና፣ ፖስታሬንጀርስ ናይሮቢ በመጨረሻም ተስከር ተጫውቼ ወደቅዱስ ጊዮርጊስ መጣው አሁን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነኝ ማለት ነው፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ የጊዮርጊስን ቤት እንዴት አገኘኸው?

ማታሲ፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ዓመቴ ነው፡፡ ስለዚህ ባብዛኛው የትምህርት ወቅት ነው ያሳለፍኩት ክለቡን፣ የክለቡን ታሪክ፣ የደጋፊዎችን ፍላጎት ብዙ ነገር ነው የተማርኩት፡፡ በርግጥ ዘንድሮ የቡድናችን ውጤት ጥሩ አይደለም እኔ በግሌ ግን ብዙ የተማርኩበት ዓመት ነው፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ የጊዮርጊስ የእናስፈርምህ ጥያቄ እንዴት መጣ?

ማታሲ፡ ጋናን ገጥመን 1-0 ካሸነፍን በኋላ ኢትዮጵያን ለመግጠም ስንዘጋጅ ነበር ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደሚፈልገኝ የሰማሁት እኔም በመጀመሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ስለምንጫወት የኔን አእምሮ ለመቀየር ታስቦ የተወራ ተራ አሉባልታና የሥነ-ልቦና ጨዋታ ነበር የመሰለኝ፡፡ ምንም መልስ አልመለስኩም ምክንያቱም በብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታ ላይ ብቻ ነበር ማተኮር የፈለኩት፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ለመግጠም በባህር ዳር በነበርንበት ጊዜ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሰዎች መጡና አናገሩኝ፡፡ ከተስከር ጋር ኮንትራት እንዳለኝ ነገርኳቸው፡፡ ከደርሶ መልሱ ጨዋታ በኋላ እነዛው ሰዎች ናይሮቢ መጡና ተነጋገርን ከኔም ከክለቤም ጋር ከተስማማን በኋላ ጊዮርጊስን ተቀላቀልኩ ማለት ነው፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ እንዳልከው በወቅቱ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በተቃራኒ እየተጫወትክ ነበር፡፡ በወሳኝ ሰዓት ተቀናቃኝ ሃገር ጋር ድርድር ማድረግ ቀላል ውሳኔ ነበር?

ማታሲ፡ ማንኛውም እግር ኳስ ተጫዋች ሁሌም ቢሆን ከሃገር ወጥቶ መጫወትን ይመኛል፡፡ እኔም የልጅነት ህልሜ ውጭ ሃገር ሄዶ መጫወት ነበር፡፡ ለረዥም ጊዜ ሳይሳካ ቢቆይም በመጨረሻ እንደቅዱስ ጊዮርጊስ ላለ ትልቅ ክለብ መጫወት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ለቤተሰቦቼ ጊዮርጊስ ሊያስፈርምኝ እንደሆነ ስነግራቸው በጣም ነበር ደስ ያላቸው፡፡ የብሔራዊ ቡድን ጓደኞቼም ቢሆኑ ሁሌም በኔ ከኬንያ ወጥቶ አለመጫወት ያዝኑ ስለነበር በጣም ነበር የተደሰቱት፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ የኬንያ ሊግና የኢትዮጵየ ሊግ ብዙ ልዩነት አለው?

ማታሲ፡ የኬንያ እግር ኳስ የበለጠ ጉልበት የሚጠይቅ ነው እዚ ደግሞ የበለጠ ቴክኒክ ላይ ያተኩራል ብዙ የኳስ ንክኪ አለ ነገር ግን ሩጫ የለም፡፡ የኬንያ ሊግ ከዚህ የበለጠ ፈጣን ነው፤ የኢትዮጵያ ሊግ ሩጫ የሌለበት ሊግ ነው፡፡ በዚህ አንድ ዓመት የታዘብኩት ይህንን ነው፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በመጫወትህ ምን ይሰማሃል?

ማታሲ፡ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ከሃገሬ ወጥቼ መጫወት የልጅነት ህልሜ ነበር፡፡ ስለጊዮርጊስ ሁሌም እሰማ ነበር ጊዮርጊስ ታላቅ ቡድን እንደሆነ አውቅ ነበር፡፡ የአፍሪካ ውድድሮችን የምትከታተል ከሆነ ጊዮርጊስን ታውቀዋለህ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በመጫወቴም ሆነ ለጊዮርጊስ በመጫወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ዘንድሮ አህጉራዊ ውድድሮች ላይ አልተሳተፋችሁም፤ ምንድን ነው የተሰማህ?

ማታሲ፡ አዎ ዘንድሮ ባልተለመደ ሁኔታ ቅዱስ ጊዮርጊስ አህጉራዊ ውድድሮች ላይ አልተሳተፈም ነገር ግን ስለሚቀጥለው ዓመት ውደድሩ ገና ስላልተጠናቀቀ መናገር አይቻልም፡፡ አሁንም ቢሆን ሻምፒዮን የመሆን ዕድሉ አለን፡፡ከደቡብ ፖሊስ፣ ከኢትዮጵያ ቡናና ከመከላከያ ጋር የጣልናቸው ነጥቦች ናቸው እንጂ ሻምፒዮናውን ቀድመን ማረጋገጥ እንችል ነበር፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ውድድሩ ሊጠናቀቅ ሶስት ጨዋታዎች ብቻ እየቀሩት አንተ ለብሔራዊ ግዴታ ወደ ግብጽ ትሄዳለህ፡፡ ሃገርህም ክለብህም ይፈልጉሃል፡፡ በዚ ወሳኝ ሰዓት ጊዮርጊስን መርዳት አለመቻልህ የፈጠረብህ የተለየ ስሜት አለ?

ማታሲ፡ እሱ ነው በጣም አስቸጋሪው ነገር፡፡በዚህ በወሳኝ ሰዓት ጊዮርጊስን መርዳት አለመቻሌ በጣም ያስቆጫል፡፡ እዚህ ሆኜ ጊዮርጊስን ብረዳው ምኞቴ ነበር፡፡ ነገር ግን  ደግሞ ሃገር ከሁሉም ነገር ይቀድማል፡፡ የኬንያ ብሐራዊ ቡድን በደብዳቤ ነው ቅዱስ ጊዮርጊስን የጠየቀው፡፡

ጨዋታዎቹ በአዘቦት ቀን ተደርገው ቢሆን ኖሮ ውድድሩ ቀድሞ ሊያልቅ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም ጨዋታዎች በሰንበት ብቻ ነበር የሚደረጉት ስለዚህ ሊጉ ሳይጠናቀቅ የዝግጅት ወቅት ደረሰ፡፡ እኔ እሄዳለው ነገርግን ጓደኞቼ እኔ ባልኖርም ምንም ለማድረግ አይቸግራቸውም፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችሁ ምን ስሜት ፈጠረብህ?

ማታሲ፡ የአፍሪካ ዋንጫ ከመጀመሩ በፊት በፈረንሳይና በግብጽ የዝግጅት ወቅት አለን ከዛም የአፍሪካ ዋንጫው አለ፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ የማንኛውም የማንኛውም አፍሪካዊ ተጫዋች ህልም ነው፡፡ ኬንያ ለረዥም ጊዜ በዚህ መድረክ ላይ አልነበረችም፡፡ ከዚህ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሁሉንም የማጣሪያ ጨዋታዎች የተጫወትኩት እኔ ነኝ፡፡ ስለዚህ አሁንም በዚህ አህጉራዊ መድረክ ላይ ሃገሬን መወከል በመቻሌ ዕድለኛ ነኝ፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ በውድድሩ ኬንያ ምን ያህል ርቀት የምትጓዝ ይመስልሃል?

ማታሲ፡ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ሁሉንም ስንጫወት ቢበዛ አንድ የዝግጅት ሳምንት ብቻ ነበር የሚሰጠን፣ አሁን ግን አንድ ሙሉ የዝግጅት ወቅት ነበረን፡፡ ከዚህ ሁሉ የዝግጅት ወቅት በኋላ የትኛውንም ቡድን ብንገጥም ቀላል ተፎካካሪ አንሆንም፡፡ ኬንያ ከየትኛውም ቡድን የተሻለ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል አላት፡፡በዛ ላይ ለማንም የማይበገር ብሔራዊ ቡድን ይዛ ነው ወደ ግብጽ የምታመራው፡፡ አሰልጣኛችን ሁሌም እንደሚለን ግብጽ የምንሄደው ለተሳትፎ አይደለም ለውድድር እንጂ፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ የማጣሪያውን ጨዋታዎች ሁሉንም ጨዋታዎች ያደረግከው አንተ ነህ፡፡ ያኔ ኬንያ ውስጥ ስለምትጫወት አሰልጣኙ ዕለት ዕለት ያህ ነበር፡፡ አሁን ግን ከኬንያ ያነሰ የእግር ኳስ ደረጃ ያላት ሃገር ውስጥ ነው የምትጫወተው፡፡ አሰልጣኙም አንተን በቴሌቪዥን እንኳ ለማየት ዕድል የላቸውም፡፡ ስለዚህ በውድድሩ ዋና ግብ ጠባቂ ሆነህ ትቀጥላለህ?

ማታሲ፡ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ከአሰልጣኙ ጋር ሁሌም ቢሆን እንገናኛለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመጣው ጀምሮ ያደረኳቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች በኋላ ለሃገሪቱ ፌዴሬሽን ሪፖርት አደርጋለው፡፡ ልክ ጨዋታው እንዳለቀ የነበረውን ነገር ሁሉ፤ ስንት ደቂቃ እንደተጫወትኩ፣ ስንት ጎል እንደገባብኝ ወዘተ በሙሉ ሪፖርት አደርጋለው፡፡ አሰልጣኙም እያንዳንዱን ነገር ያውቃሉ ለምሳሌ ሁለተኛ ዙር ፕሪሚየር ሊግ ከተጀመረ በ11 ጨዋታዎች 3 ግብ ብቻ ነው የተቆጠረብኝ ይህን ሁሉ ያውቃሉ ስለዚህ የመጀመሪያ ተሰላፊ መሆኔ ጥርጥር የለውም፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ የስትዋርት ሃል መሰናበት በጊዮርጊስ ውስጥ የፈጠረው ስሜት

ማታሲ፡ ጥሩ አሰልጣኝ ነበሩ፡፡ እኔን በተለይ እንደአባት ይመክረኝና ያበረታታኝ ነበር፡፡ የችሎታ ጉዳይ ሳይሆን የኛ የሜዳ ላይ ውጤት ደስ ስላላሰኘው መሄድ ፈለገ፣ ውሳኔውን ታከብርለታለህ፡፡ የክለቡ አመራሮች መጥተው አወያይተውን ነበር፡፡ የራሱ ውሳኔ ስለሆነ ምንም ማድረግ አልተቻለም፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ የቋንቋ ችግር ከተጫዋች ከአሰልጣኝ ጋር

ማታሲ፡ በፍጹም የበረኛ አሰልጣኙ ኤይሜ ምስራቅ አፍሪካዊ ነው ስዋሂሊ ይችላል፡፡ በእንግሊዝኛም ከሱጋ እንግባባለን፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ አሰልጣኛችንም እንግሊዛዊ ነበሩ፡፡ በጨዋታ ላይ ደግሞ ከአስቻለው፣ ከከሪም ጋር በእንግለዝኛ እንግባባለን በተጨማሪ እኔም ወደኢትዮጵያ ስመጣ በጣም የሚያስፈልጉኝን ቃላት አጥንቻለው፣ ና፣ ሂድ፣ ስጠኝ፣ ምታ ወዘተ ማለት በደንብ እችላለው፤ ስለዚህ ምንም ችግር የለብኝም፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ስለደጋፊው ምን የምትለው አለህ?

ማታሲ፡ ደጋፊዎቹ ሁሌም የሚገርሙ ናቸው፡፡ ስናሸንፍም ስንሸነፍም ሁሌም ከጎናችን ናቸው ይሄ ብዙ ቦታ አልተለመደም፡፡ ቡድኑ ውጤት ርቆት ጨዋታ ሲኖር ግን ደጋፊው ሙልት እንዳለ ነው፡፡

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ኑሮ እንዴት ነው?

ማታሲ፡ እንደመጣው በተለይ ምግብ መልመድ በጣም ተቸግሬ ነበር፡፡ እኔ የለመድኩት ኡጋሊ ነው፤ እንጀራበሸክላ ጥብስ በየት በኩል ይግባልኝ

አቢሲኒያ ቢዝነስ ኔትወርክ፡ ከአፍሪካ ዋንጫውስ በኋላ ዕቅድህ ምንድን ነው?

ማታሲ፡ ከጊዮርጊስ ጋር ኮንትራት አለኝ፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው አቋሜ እሚፈልገኝ እንኳ ቢመጣ ከኔጋ ሳይሆን ከጊዮርጊስ ጋር ነው የሚነጋገረው፡፡ ጊዮርጊስ መሸጥ ከፈለገ ያስተላልፈኛል ማቆየት ከፈለገም ያቆየኛል፡፡ እኔ የአፍሪካ ዋንጫው ምርጥ በረኛ ሆኖ ውድድሩን መጨረስ ከዛም ከጊዮርጊስ ጋር ቆይቼ በርካታ ድሎችን ማጣጣም ነው ሃሳቤ፡፡ 

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *